|
|
|
ከኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት
የተሰጠ የሐዘን መግለጫ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ባደረባቸው ህመም በውጭ ሀገር ህክምና ሲከታተሉ ቆይተው ሰኞ ነሐሴ 14 ቀን 2004 ዓ.ም ከምሽቱ አምስት ሰዓት ከአርባ (5:40) ላይ ህይወታቸው ማለፉን የሚገልጽ ዜና ሲገለጽ ኢትዮጵያ ብሎም አፍሪካ ታላቅ ሰው እንዳጣችና በዚህም የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት የተሰማዉን ከፍተኛ ሀዘን ይገልጻል፡፡
ገና በትጥቅ ትግሉ ወቅት በወጣትነት እድሜያቸው ለኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ጥቅም ትግል የጀመሩ ታላቅ መሪያችን ባለፉት 21 አመታት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ ለማድረግ ያለመታከት ቀን ከሌሊት ሰርተዋል፡፡በአሁኑ ወቅትም በተጨባጭ የተመዘገቡ የሰላም የልማትና የዲሞክራሲ ውጤቶች እንዲጠናከሩና በመላ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ መነሳሳትን የፈጠረውን የአምስት አመቱን የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ በመንደፍ ለተግባራዊነቱ ያላሰለሰ ጥረት ያደረጉ ታላቅ መሪያችን ነበሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በዓለም ዓቀፍ መድረኮች ኢትዮጵያንና አፍሪካን በመወከል ለአፍሪካ ሠላምና መረጋጋት መስፈን እንዲሁም የኢኮኖሚ ዕድገት መመዝገብ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ አገራችን ብሎም አፍሪካ ያፈራቻቸው የምዕተ አመቱ ብርቅዬ መሪያችን ነበሩ፡፡
የብሔርብሔረሰቦች፣እኩልነት፣ልማት፣ዲሞክራሲና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን፣የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንዲስፋፋ ያላሰለሰ ጥረት ያደረጉ ታላቅ መሪ እንደመሆናቸው ዜና እረፍታቸው ለኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት ሰራተኞች ታላቅ ድንጋጤና መሪር ሐዘን ፈጥሮብናል፡፡
ውድ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ የአገራችን ጠላት የሆነውን ድህነት እየተዋጋን ባለንበት በአሁን ወቅት ታላቁ መሪያችን በታሪክ አጋጣሚ ብናጣቸውም በእሳቸው ሀሳብ አፍላቂነት የተጀመሩትን የልማት እና የዲሞክራሲ ጉዞአችንን በበለጠ በማጠናከር የኢትዮጵያን ሕዳሴ በማረጋገጥ ታላቁ መሪያችን የጣሉብንን አደራ በመወጣት ታሪካቸው ህያው ሆኖ እንዲኖር ማስቻል ይኖርብናል፡፡
በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ቤተሰቦችና ወዳጆች መፅናናትን ይመኛል፡፡
ነሐሴ 15/2004 ዓ.ም
|
|